የኮንታ ዞን ካቢኔ አካላት በዛሬው ዕለት ባደረጉት መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውሳኔ አስተላልፈዋል። በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል በተያዘው በጀት ዓመት ለበለጠ ውጤታማነት መትጋት እንደሚገባ ተገልጿል። የዞኑ ካቢኔ አካላት በመጀመሪያ ደረጃ የተወያዩት የ2018 በጀት ዓመት የበጀት ማጠቃለያን በተመለከተ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በጀትን በተገቢና በጥንቃቄ በመምራት መሠረታዊ የህዝቡ የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚመልሱ ሰፊ ስራዎች የተሰሩበት ዓመት እንደነበር ቀርቧል። በተለይም ግዴታ ወጪዎችን በተገቢው ከመምራት ባሻገር መሠረታዊ የህዝብ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንገድ፣ በውሃ፣ በጤና በትምህርት፣ በግብርና እንዲሁም በተቋማት ግንባታ እና መሠል ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱ የቀረበ ሲሆን ከመደበኛ ስራዎች ባሻገር ሀገራዊ ኢንሼቲቭ ተግባራት በውጤታማነት የተጠናቀቁበት ወቅት እንደሆነ አንስተዋል።የዞኑ ካቢኔ አካላት ዓመቱ በአመራር ቁርጠኝነትና ቅንጅት እንዲሁም በህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ ፍትሃዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የተፈፀሙበት መሆኑን ገልፀው ይህንን በማጠናከር በተያዘው በጀት ዓመት ለበለጠ ውጤታማነት መትጋት ይገባል ብለዋል።

ካቢኔው በሁለተኛ አጀንዳነት በ2019 በጀት ዓመት በአስቸኳይ በሚያስፈልጉ ግዥዎችና የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት መጀመር ባለባቸው ካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ ውይይት አድርጓል።በዚህም ምንም እንኳን የሀብት እጥረቱ ቀላል ባይሆንም ትኩረት የሚሹ አካባቢያዊ ችግሮችንና እንዲሁም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል በልዩ ትኩረት መፈፀም ያለባቸው ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን እርሻ ትራክተር በቁጥር ፦8ገልባጭ ተሽከርካሪ፦1አንቡላንስ :-1ለቢሮ አገልግሎት የሚሆን 2 ተሽከርካሪ ግዥ ፍላጎት ለክልሉ እንዲቀርብ የተወሰነ ሲሆን ከካፒታል ፕሮጀክቶችም አንፃርየሞዴል ቅ/መደበኛ ት/ቤቶች 6 ፣በክልሉ በ2ኛ ምዕራፍ በ14 ከተማ አስተዳደሮች ከሚጀመሩ መሶብ ማዕከላት አንዱ የሆነው የጪዳ ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ፣ ለቀጣይ 2019 ሀገር አቀፍ 12ኛ ክፍል የበይነ መረብ ፈተና በሁሉም 2ኛ ደ/ት/ቤቶች ለመጀመር መሟላት ባለባቸው ጉዳዮች ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ተላልፏል።ይህም በከፍተኛ ፍጥነት የሚጨምረው ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበቱ ውሎ ባደረ ቁጥር በበጀት ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ከወዲሁ ለማስኬድ ትኩረት ተሰጥቷል ።

በመቀጠልም ካቢኔው የብሄረሰቡን ባህል ታሪክና ቋንቋ ማልማት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔ ሰጥቷል። በአራተኛ አጀንዳነት የዞኑን አቅምና መፃዕ እድል የሚለይና ዘላቂ እድገት የሚጠቁም የመካከለኛ ጊዜ የልማት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ላይ በመወያየት ይህንን የሚሰሩ አጥኚ ቡድን ተደራጅቶ እንዲፈፀም ወስኗል። ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።