• የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ላይ መኖር ከጀመረ ብዙ ሺህ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን እያንዳንዱ ትውልድ የሚኖርበትን አከባቢ ተፈጥሮ ባደላቸው የዕውቀት ችሎታና በየገጠመኞች ባከማቸው ልምድ እየታገዘ መሠረታዊ የሆኑትን ፍላጎቶቹን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ  ይገኛል፡፡ በዞናችን በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ልምዶች በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ዕውቀትና ክህሎቶች የፈጠራ ውጤቶች በየጊዜው እያሻሻሉና በውጤቱም እየተጠቀሙ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡
  • በዞናችን ውስጥ ከሚገኙ 62 ቀበሌዎች በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ 4,000 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የኦሽካ ዴንቻ የብረት ማዕድን ክምቸት ከ80% በላይ ነው፡፡
  • ፃራዎች የብረት ማዕድንን ከአፈር ውስጥ ቆፍሮ ከማውጣታቸው በፊት እዛ አካባቢ ላይ ብረት መኖሩንና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጉድጓድ ይቆፍሩና በደረታቸው ተኝተው ጆሮአቸውን በተቆፈረ ጉድጓድ ላይ ተክለው ያዳመጡታል፡፡ በመቀጠልም ብረት  መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ ሹል እንጨት በመሰካት ምልክት አድርገው ያልፋሉ፡፡
  • በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተወሰነ ርቀት ከተጓዙ በኋላ  በአንድ ዛፍ ጥላ ስር ተሰባስቦ ይወያያሉ፡፡ የውይይቱ አላማውም አፈር የመለየት ስራ ለመስራት ነው፡፡
  • ይህ የ2ኛው ስራ የሚከናወነው ከአፈር የተሰራውን ትልቅ ገንቦው በእሳት ላይ በመጣድ በብዙ ፍተሻና ውጣወረድ ተቆፍሮ የመጣውን አፈር በገንቦው ውስጥ ይጨምሩበታል፡፡
  • ከፍተኛ የማገዶ እንጨት በመጨመርና በስልቻ(ወናፍ) ተራ በተራ እየነፉ የመንደቅደቅ ድምዕ ማሰማት ሲጀምር እና በእንስራዉ ጫፍ ከፍተኛ እሳት ስወጣ አንድ የበግ ሙክት አርደው ደሙን በገንቦ ውስጥ እና ውጭ ካፈሰሱ በኃላ ገንቦውን አውርደው የተቀቀለውን ነገር እያወጡ መሬት ላይ ይከምራሉ፡፡ በመቀጠልም በስለታም ቆንጭራ እያንዳንዱን እየጠረቡ ቅርፍት መሣይ ነገር ከላዩ ላይ እየገፈፉ በማፅዳት ይለያሉ፡፡ ሁለተኛዉን ተግባራቸውን በዚህ መልክ ካጠናቀቁ በኃላ ሦስተኛዉን ተግባር ይጀምራሉ፡፡ ይህም ተነጥሮ የተለያዩ ብረቶችን በእሣት በማጋየትና በመቀጥቀጥ የተለያዩ ስለታም መሣሪያዎችን ማለትም ቢለዋ፤ ጦር፤  የእርሻ መሣሪያዎችን፤  በእግር የሚደረጉ ጌጣጌጦችን፤ሰይፍ፤የትንፋሽ መሣሪያ፤ መጥረቢያ፤ገጃሞ ወዘተ…. በመስራት ወደ ተለያየ አካባቢዎች ተዘዋውረው ይሸጣሉ፡፡ በሚያገኙት ገቢም ይተዳደሩበታል፡፡ እንግድህ ይህ ነው የኦሽካ ዴንቻ ባህላዊ የሳይንስ ግኝት ማለት፡፡
  • ሀገር በቀል እውቀቶችን ፈጥረው ጠብቀው እንዲሁም እየተጠቀሙባቸው ለትውልድ ያስተላለፉት አያት ቅደመ አያቶቻችን ዛሬ እንደ ትልቅ ሀብት እንድንጠቀምባቸው ረድተውናል፡፡ 
  • የኮንታ ብሔረሰብ ባህላዊ ዳኝነት- ሻቲንታ ዛባ ይባላል፡፡

የባህላዊ ዳኝነት በህዝቡ ተመራጭነት ያለዉ  የመሆኑ ሚስጥር

  • ባህላዊ ዳኝነት እርቁ የሚካሄደው በበዳይና ተበዳይ የጋራ ስምምነት በተመረጡ ሽማግሌዎች የሚዳኙ መሆኑ፤
  • በባህላዊ ዳኝነት የሚሰጠው ውሳኔ ይቅርታ እና ምህረት ያለው መሆኑ፤
  • በባህላዊ ዳኝነት የሚሰጠው ውሳኔ ቂምና በቀል የሌለው፣ ወደፊት በማኅበራዊ ህይወታቸው ተስማምተውና ተግባብተው እንዲኖሩ የሚያደርግ  መሆኑ፤
  • በባህላዊ ዳኝነት የሚሰጥ ውሳኔ በዳይን ለእሥራትና ለእንግልት የማይዳርግ መሆኑ፤
  • ባህላዊ ዳኝነት በክስ አቤቱታና ሙግት የሚጠፋውን ጊዜና ሀብት ከብክነት የሚያድን በመሆኑ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ይልቅ የበለጠ ተመራጭ የሚያደርግ ነዉ፡፡
  • የባህላዊ ዳኝነትና ግጭት አፈታት  ለአብነት የቀረቡ

የኮንታ ብሔር በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ አንዱ የዘመን መለወጫ ወይም የሕንግጫ በዓል ነዉ፡፡ ስለ ዘመን መለወጫዉ ከማዉራታችን በፊት በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ ሶስት የተለያዩ ትርጓሜዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፤ እነሱም ሙጬ፣ ቶኪቤአ እና ሕንግጫ ሲሆኑ ከህዝቡም ዉስጥ አንዳንዶቹ ዘመን መለወጫን ሙጬ (Muuc’e) ሌሎቹ ደግሞ ቶኪ ቤአ (Tooki-Be’a) አብዛኛዉ የሕብረተሰብ ክፍል ህንግጫ ( Hingic’aa ) በማለት የየራሳቸዉን ትርጉም እየሰጡ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በዓሉን እያከበሩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ህንግጫ ባህላዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የትርጉም አሰጣጡ ቀደምት አባቶች ሲያከብሩ የሰጡት ስያሜና ትዉፊት በተግባር ባለመዋሉ የጋራ የሆነ ስያሜ ሳይሰጠዉ ቢቆይም ‹‹ሙጬ ›› ማለት ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 5/6 ድረስ ያሉ ቀናትን የሚያመላክት ሲሆን በእነዚህ ቀናት ዉስጥ በተለይም ጤፍ ቢዘራ የማይበቅልና ቢበቅልም እንኳን ከግንዱ ተቆርጦ የሚወድቅ እንዲሁም ሳያድግ ቀጭጮ ይቀራል ተብሎ ስለሚታመን ወቅቱ ‹‹ ሙጬ ›› ተብሏል፡፡

‹‹ ቶኪ ቤአ ›› ማለት ደግሞ ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ማለትም “ትርኳሽ” በሚወጣበት ቀን የቤተሰብ አባላት በሙሉ ጠግበዉ ካላደሩ ‹‹ቶኪ ቤአ›› የሚባል መንፈስ በዕለቱ መዝኖ በማየት ዓመቱን በሙሉ እንደተራበና እንደቀለለ ይከርማል ተብሎ ስለሚታመን ያንን ለማመልከት የተጠቀሙት ቃል ስለሆነ የዘመን መለወጫ አንዱ ክዋኔ ነዉ፡፡ በመሆኑም ‹‹ ሕንግጫ ›› የሚለዉ የብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል እንደሆነ የዕድሜ ባለፀጋዎችና የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍቶች ይመሰክራሉ፡፡ የኮንታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ማክበር የጀመረዉ በኦሞ፣ በጎጀብ እና በዝግና ተፋሰስ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዓሉን ሲያከብሩ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ ሆኖም በዓሉ መቼና እንዴት ተጀምሮ እያደገ እንደመጣ ትክክለኛውን ጊዜ የሚጠቁም የጽሑፍ መረጃ ባይኖርም ለበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ የራሱ አመልካች መረጃዎች እንዳሉ ከቀደምት አባቶች በአፈ-ታሪክ እና አንዳንድ የጽ ሑፍ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም በኮንታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም የመጀመሪያው የአራ ዘረ-ግንድ ቀዳሚ ንጉስ “ካቲ ኤማዶ” ዘመነ መንግስት በ12ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ ከጎረቤት ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን እያከበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆኑ በታሪክ ይነገራል፡፡ የህንግጫ በዓል ታሪካዊ ዳራ ባህልና ታሪክ ባህልና ታሪክ የህንግጫ በዓል አከባበር በኮንታ ! የህንግጫ በዓል አከባበር በኮንታ ! የበዓሉ አከባበርና ዕሴት ‹‹ህንግጫ›› ማለት እንደ ብሔሩ አባቶችና የታሪክ ምሁራን አገላለጽ የሁለት ቃላት የ‹‹ሂን›› እና የ‹‹ጊጫ›› ዉህድ ነዉ፡፡

‹‹ሂን›› ማለት ወደዚያ አስፋ/ፊ ሲሆን ‹‹ጊጫ›› ማለት አሳምር፣ ጥረግ፣ አጽዳ፣ ፋቅ (Giid’ara) የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በመሆኑም ከዕለቱ በዓል ጋር የሚያያዝበት ምክንያት ጎረቤት በዓሉን አብሮ ለመታደም፤ወጣቶች በበዓሉ ወቅት ለጭፈራ እና ለምርቃት ሲመጡ ባማረና ጽዱ በሆነ አካባቢ እንዲያከብሩ እንዲሁም በዓሉ ሲከበር እንግዳ ለመቀበል ለመመራረቅ ከየጎረቤቱ አዲስ ዓመትን ለማክበር እና አዲሱ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከርሃብ ወደ ጥጋብ ሲሸጋገሩ ብሩህ ተስፋን ሰንቀዉ በእርቅና በጥጋብ ለምድሪቱ ሠላምን፣ በረከትን፣ ፍቅርን፣ ጤንነትን፣ በመመኘት የሚቦርቁበት አካባቢ መሆኑን ያሳያል፡፡ አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ አመልካች በመሆኑ ያንን ለማመልከት የተጠቀሙት ቃል ሲሆን ከበዓሉ ዝግጅት ጋር ይያያዛል፤ይኸዉም ደጃፍን አስፍተህ/ሽ አጽዳ/ጅ /kariya/ Aassade Giic’c’aa፣ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ለበዓሉ ከሚዘጋጅ የምግብ ዓይነቶች ዉስጥ አንዱ አንጮቴ ወይም Ushshushi ya Giic’c’aa እና በበዓሉ ተዉቦና ደምቆ ለመታየት እንሶስላ ወይም wusoluwa Giic’aa ከሚለዉ ጋርም የተያያዘ ነዉ፡፡

የኮንታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለዉ ሲሆን የዘመን አቆጣጠሩ የመጀመሪያ የመስቀል ወር / Mask’ala Aginaa / ይባላል፡፡ በህንግጫ በዓል አከባበር ወቅት ወጣቶች ከሚጫወቱት ጨዋታ “Hoyabee salo, wod’aassaa wosikkee , andoli bole, wohee baabo baabo, koole kooli godaa” ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የህንግጫ በዓል እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ጎረቤት የተጣላ ሳይታረቅ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ስለሌለበት የተጣሉ ግለሰቦች በጎረቤት ሽማግሌ ይቅር ለእግዚአብሔር ይባባላሉ፡፡ ከቤት ርቆ ያለም ሆነ ከቤት ዉጭ ያለ ማንኛዉም የቤተሰብ አባል ወደቤት ሳይገባ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” ስለማይወጣና ዉጭ ከቀረ በዚያዉ ይቀራል ተብሎ ስለሚታሰብ የግድ ወደቤት ከገባ በኋላ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” በመያዝ “እርኩስ መንፈስ ዉጣ” እያለ ከዚህ በታች በተገለጸዉ መልክ ይፈፀማል፡፡ የትርኳሹን እጄታ በመያዝ እና በማወዛወዝ ወደ ዉጪ የሚያወጣዉ አባወራ ለአዲሱ ዓመት ያደረሰዉን ፈጣሪ እያመሰገነና መጪዉ ዘመን የደስታ፣ የፍቅር፣ የጤንነት፣ የሠላም፣ የአንድነትና የጥጋብ እንዲሆን እየተማፀነ እቤት ዉስጥ ያለዉ የአሮጌዉ ዘመን ክፉ መንፈስ እንዲወጣ እያንዳንዱን የቤት ዉስጥ ቁሣቁስ ለአብነት መኝታዉን፣ መከታዉን፣ ምሰሶዉን፣ ወጋግራዉን፣ የከብቶችን በረት፣ ( ከበሬ ጫንቃ ከላሞች ግት) መዉጫ በሩን በትርኳሹ እየነካ ‹‹የረሃብ የበሽታ የጥላቻ ክፉ መንፈስ ከዚህ ቤት ዉጣ›› እያለ ካዳረሰ በኋላ ትርኳሹን ከቤት አዉጥቶ ወደ ዉጪ አርቆ ይወረዉራል፡፡

ትርኳሹ (Ts’iifaa) በሚወጣበት ቀን በዕለቱ ለእራት የሚዘጋጅ ምግብ ማብሰያዉን ሞልቶ ይዘጋጃል፤እንዲሁም በቤት ዉስጥ ያሉ የምግብም ሆነ የዉሃና የወተት ዕቃዎች በምግብ፣ በዉሃና በወተት ተሞልተዉ እና ተከድነዉ ማደር አለባቸዉ፤ምክንያቱም እነኝህ ቁሳቁሶች ጎደሎ ሆነዉ የሚያድሩ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ ችጋርና ርሃብ ከቤት አይወጣም ተብሎ ይታመናል፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ በአካባቢዉ ታዋቂ ወይም የዕድሜ ባለፀጋ በሆኑ አባቶች ቤት በመጀመሪያዉ ቀን በጋራ ይከበራል፤ በበዓሉ አከባበር ቀን የሚወጣዉ ትርኳሽ በችቦ መልክ ሣይሆን በምድጃ ዉስጥ እየነደደ ካለዉ የማገዶ ጉማጅ ከነፍሙ ተመዞ በመያዝ ይወጣል፡፡ የዚህ ጉማጅ ስም በአካባቢዉ አጠራር “ፂፋ” ይባላል፡፡ ከዚያም በኋላ የቤተሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ ጎረቤቶች እንደየ ዕድሜአቸዉ ቦታ ቦታቸዉን ከያዙ በኋላ የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ ከ1-3 በሚደርሱ ሽማግሌዎች ምርቃት ይደረጋል፡፡ ምርቃቱም ፡ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ቀርበዉ “ቦርዴ” በትልቅ እንስራ አሙልቶ በማፍሰስ በሴቶች እልልታ ታጅቦ ጠላዉን ለእያንዳንዱ ታዳሚ በማዳረስ በሚከተለዉ መልኩ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡

ከተሞላዉ እንስራ በዋንጫ የተቀዳ ጠላ በመጀመሪያ የተሰጣቸዉ የዕድሜ ባለፀጋዎች እና መራቂዎች በሚከተለዉ መልክ ይመርቃሉ፡ • ‘በአሮጌዉ ዓመት ሲያጣላንና ሲያጋጨን የነበረዉ ክፉ መንፈስ ከመሃላችን ፈጣሪ ያርቅልን’ ! • ‘ይህ ጠላ ሞልቶ እንደፈሰሰ ሁሉ ጤንነት፣ ፍቅር፣ ሠላምና ጥጋብ በሃገራችን፣ በአካባቢያችንና በሰፈራችን እንዲሁም በእያንዳችን ቤት እንዲዚህ ሞልቶ ይፍሰስ’ ! • ‘አዲሱ ዓመት የሕዝቡ እና የመንግስት አንደበት የሚጣጣምበት ዘርተን የምንቅምበት፣ ወልደን የምንስምበት፣ ነግደን የምናተርፍበት፣ ከቤት የወጣዉ በሰላም የሚመለስበት፣ ያፈራነዉን በሰላምና በፍቅር የምንበላበት ዘመን ያደርግልን’ ! • ‘በአዲሱ ዓመት ስትወጡ እንቅፋት አይምታችሁ፤ ስትናገሩ እዉነተኛ ሃሳብ አይጥፋባችሁ፤ ፍቅራችን እንደ ሰማይ ጉም እንደ ምድር ሰርዶ እንደ ጉንዳን ሕብረትና አንድነት እግዚአብሔር ያድለን ! በመጨረሻም ከእኛ የተረፈዉን እግዚአብሔር ይመርቃችሁ’ ! በማለት ያጠቃልላሉ፡፡

 

  • የኮንታ ባህል ማዕከልና ሙዚዬም ተገንብቶ  ሥራዉን የጀመረዉ  በ2011ዓ.ም ነው፡፡
  • ባህል ማዕከሉ የኮንታ ሕዝቦች የባህል፣ የታሪክ፣ የቅርስ ጥናትና ምርምር ማዕከል በመሆን ያገለግላል፡፡
  • ማዕከሉ የቤተ መጽሐፍት፤ የሙዚዬምና የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሰል አገልግሎት እየሰጠ  ይገኛል፡፡

በእናትነት ወርቅነት አጊጣ ከአራስ ቤት ስትወጣ… በሙሽርነት ወገቧን ታጥቃ ከጫጉላ ስትመለስ… አልያም አዲስ የኑሮ ስኬትን በአዲስ ልብስ ስታበስር፤ በኮንታ ምድር የደስታ መድረክ ይዘረጋል። ይህ የሴቶች ብቻ ዓለም፤ የፍቅርና የአንድነት ማሳያ “ሶፌ” ይባላል። የቤት_ውስጥ_ድግስና_ድምቀትገና ከማለዳው የቤቱ ደጅ በሳቅና በጨዋታ ይሞላል። አየሩ በጎመን ኡስታ እና በሀንጮተ ኡስታ መዓዛ ይታወዳል፤ ፅዋውም በጣፋጩ ቦርዴ ይሞላል። ሶፌ የብቻ ደስታ አይደለም፤ የአንዱ ስኬት የሁሉ ነውና ሴቶች በመካከላቸው አቅፈው፣ በፍቅር ከበው በክብር ያስውቧታል።

ድግሱ በቤት ብቻ አይወሰንም! ተመሳሳይ አዲስ ልብሳቸውን ለብሰው እንደ ጽጌረዳ አብበው ወደ ገበያ ይወጣሉ። የገበያው መተላለፊያ በነርሱ ውበት ይደምቃል። በጋራ ቦርዴ እየተጎነጩ፣ ቅመማ ቅመሞችን እየቆረጠሙ፣ “አፍ ለአፍ” እየተገጣጠሙ የልብን ምስጢር ያወጋሉ።ይህ ጉዞ ለኮንታ ሴቶች ተራ ሽርሽር አይደለም፤ የነፃነታቸው አዋጅ፣ የእህትማማችነታቸው ማህተም እንጂ!የሰላም_ስንብትፀሐይ አዘቅዝቃ ወደ ተራራው ስትጠጋ፣ ደስታቸውን ቋጥረው ወደ ቤት ይመለሳሉ። በቡና ቁርስ ታጅበው በምርቃት ተሞልተው “ለቀጣዩ ሶፌ ያድርሰን” እየተባባሉ በፈገግታ ይሰነባበታሉ።

ዞሃ – በኮንታ ብሄረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የምሰጠው ረጅሙ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ነው በኮንታ ብሄረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የምሰጠው በቁመቱ ረዘመ ያለው “ዞሃ” የተሰኘ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ በቁጥር ሦስት ስሆን እያንዳዳቸው የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን የያዙ ናቸው። ከጥንት ጀምሮ ማህበረሰቡ በደስታና በሀዘን ማድመቂያ:- በልዩ ልዩ ስነ-ስርዓቶች/ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዞሃን በስፋት እየተጠቀመበት መጥቷል። ዞሃ የታሪክና የባህል መገለጫ ሆኖ የኮንታ ሕዝብ ማንነትን የሚያንጸባርቅ ውድ ቅርስ ነው !!       

                                                   ስለ ኮንታ ባህል ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ
                                                     contact: +251915675187 
                                                     email : abebed602@gmail.com