
መንግሥት ሌብነትን እና ሕገወጥነትን ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ ነው ፡፡
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱ እና የሀገር ሀብት በሚመዘብሩ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታወቀ። የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፈጣን ልማትና ዕድገት እንድታረጋግጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ሰፋፊና አስደናቂ ሀገራዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ግን ይህ ውጤት ጉዞው አልጋ በአልጋ እንዳልነበር አመላክተዋል ። ከተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ባሻገር፣ ሕገ-ወጥነት እና የሙስና ተግባራት የልማቱ ዋነኛ ፈተና ሆነው መቆየታቸውንም ክብርት ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ የሕገ-ወጥነት ችግር በአንድ ወገን ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጠቃልል መሆኑን ገልጸው ከውስጥም ከውጪም ያሉ ኃይሎች በተደራጀ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በልማት ድርጅቶች፣ በመንግሥት መዋቅር፣ በግለሰቦች እና በተገልጋዮች ጭምር በተደራጀ መንገድ በስፋት የሚታይ ነው።እነዚህ አካላት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከቁጥጥር ውጭ ለማድረግ በፋይናንስ እና በንግድ ሥርዐቱ ውስጥ ሰርገው በመግባት የኢኮኖሚ አሻጥር ሲፈጽሙ ቆይተዋል” ያሉት ወይዘሮ እናትዓለም፤ ድርጊቱ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ፣ የዋጋ ንረትና ኮንትሮባንድ እንዲባባስ እንዲሁም በፍጆታ እቃዎች ላይ ሰው ሠራሽ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን አስታውቀዋል። ይህንን የተደራጀ አሻጥር ለመግታት መንግሥት እና የሚመለከታቸው የሕግ አካላት ባከናወኑት ሰፊ ኦፕሬሽን አሻጥሩን ማክሸፍ መቻሉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ እና አስተዳደር አካላት እንዲሁም የሕዝብ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ ሌቦችን በማጽዳት ረገድ መንግሥት ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ያስታወቁት ወ/ሮ እናትዓለም በሕዝብ ሀብት ላይ ምዝበራ የፈጸሙ እና ተቋማዊ አሻጥር በሠሩ አመራሮች እና ሌሎች የጥቅም ትስስሮችና ድርጅቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል። በተለይም በሚከተሉት ቁልፍ ዘርፎች ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ሰፊ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት ሰፍኗል ሲሉ ገልጸዋል፡
በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ እና አስተዳደር አካላት፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች ውስጥ የተፈጸሙ ዋና ዋና የሙስና እና አሻጥር ወንጀሎችን ለማረም በተወሰዱት ሰፊ ኦፕሬሽኖች እና ሕግ የማስከበር እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ማሻሻያውን ለማደናቀፍ በማሰብ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠርና ዋጋ እንዲንር ሲያደርጉ የነበሩ 13 አቅራቢ ድርጅቶች ባለቤቶች ላይ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፤ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩ ከ7 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶችና መጋዘኖች ላይ የማሸግ እርምጃ ተወስዷል።በፋይናንስ ተቋማት እና የገንዘብ ዝውውር፡ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሐዋላ እና በጥቁር ገበያ ተሳታፊ የሆኑ 169 ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተደራጀ መንገድ ከንግድ ባንክ ደንበኞች አካውንት ላይ በማጭበርበር ገንዘብ የወሰዱ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የባንክ ሒሳባቸው እንዲታገድ ተደርጓል።
ለሕገ-ወጥ ዝውውር ሽፋን ይሰጡ የነበሩ 7 የክሪፕቶ ካረንሲ መተግበሪያዎች በሀገር ውስጥ እንዳይሠሩ ሙሉ በሙሉ ታግደዋል፤ ምርት ልከው የውጭ ምንዛሬ ተመላሽ ያላደረጉ 29 ላኪ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም የህግ ተጠያቂነት ሰፍኗል። በቤቲንግ እና ፊንቴክ ቢዝነሶች፡ የደንበኞችን መረጃ በመደበቅ መንግሥትን ግብር ያጭበረበሩ፣ ገቢያቸውን የሰወሩ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በፈጸሙ 38 የቤቲንግ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዶ ባለቤቶቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ የእነዚህ ሕገ-ወጥ ተቋማት የባንክ ሒሳብ ታግዷል፤
በማዕድን ዘርፍ ሕገ-ወጥ ዝውውር፡ የወርቅ ምርትን ከገበያ ውጭ በኮንትሮባንድ በማስወጣት ወንጀል የተሳተፉ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችን፣ አምራቾችን እና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 183 ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ ተደርገዋል። በወንጀሉ የተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች ከሀገር እንዲወጡ ተደርገዋል፤ ሕገ-ወጥ ወርቅ፣ የወርቅ ሚዛንና ማቅለጫ፣ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።ከነዳጅ አቅርቦት እና ሎጂስቲክስ አንጻር፡ በሕገ-ወጥ መንገድ የሽፋን ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት፣ ነዳጅ በመደበቅ እና አየር በአየር በመሸጥ ወንጀል የተሳተፉ 38 የመንግሥት አመራሮች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ ከ650 በላይ ግለሰቦች፣ ማደያዎች እና አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ የህግ እርምጃ ተወስዷል።
በአፈር ማዳበሪያ ግዢ አሻጥር፡ በተቋሙ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ጥራት የጎደለውና ጊዜው ያለፈበት የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ ሆን ብለው ችግር በፈጠሩ የግብርና ሚኒስቴር አመራሮች ላይ የወንጀል ተጠያቂነት እርምጃ ተወስዷል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEP)፡ ተገቢው መመሪያ በሌለበት ሁኔታ ከ36 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ጋር ሕገ-ወጥ የኃይል ሽያጭ ውል የፈጸሙ 4 ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት የፈጸሙ ድርጅቶች እና ግለሰቦችም እንዲሁ በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የሰዎች ዝውውር የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሲስተምን በማዛባት እና ጉቦ በመቀበል ወንጀል የተሳተፉ 8 ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። እንዲሁም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ 44 ደላሎች እና አዘዋዋሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ ሕገ-ወጥ ፈቃድ የነበራቸው ተቋማት ሙሉ በሙሉ ታሽገዋል።በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ፡ የግብር ውሳኔዎችን በመቀነስ፣ ሐሰተኛ ደረሰኞች በማወራረድ፣ እና በሲስተም መረጃ በማጥፋት የመንግሥት ገቢን ባሳጡ አካላት ላይ ኦፕሬሽን ተካሂዷል። በራሳቸው፣ በዘመድ እና በሹፌሮቻቸው አካውንት በመጠቀም የጥቅም ትስስር የፈጠሩ 109 ተጠርጣሪዎች ተለይተው ከእነዚህ መካከል 91 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
መንግሥት የልማት እንቅፋት የሆኑትን ሙስና እና ሌብነት እንደማንኛውም ፈተና በጽናት እየተጋፈጣቸው መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።መንግሥት ሌብነትን ለማጥፋት ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋት እና በዲሲፕሊን የታነጸ አመራር ለመገንባት ቁርጠኛ ነው” ያሉት ወይዘሮ እናትዓለም፤ ሕዝቡ በስፋት የሚያነሣቸውን “ሌብነትን አስቁሙልን” ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመረዉ ጠንካራ እርምጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ማኅበረሰቡ ሙስናን በማጋለጥ፣ ሕጋዊ መብቱን በመደለያ ባለመጠየቅ እና ከሕገወጦች ጋር ባለመተባበር ከመንግሥት ጎን በመቆም ሀገርን ከሕገወጥነትና ሙስና የመከላከል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ህዩዋ…ባላ ህዩዋ…. እንኳን አደረሳችሁ፡፡
ጳጉሜ 1 በታላቅ ድምቀት የሚከበረው “ህንግጫ” የልምላሜው መልክ፤ የኮንታ ብሔረሰብ አዲስ ዓመት፤
የኮንታ ብሔረሰብ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችና ዕሴቶች ባለቤት መሆኑ እሙን ነው፤ ከእነዚህ ውብ ዕሴቶች አንዱ የሆነው የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ/ህንግጫ/ በዓል አንዱ ነው።የኮንታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ /ህንግጫ/ በዓል በብሔረሰቡ ዘንድ በየዓመቱ በታላቅ ጉጉት ተጠብቆ የሚከበር ልዩ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ነው፡፡ እሴቱ ሳይጎድልና ውበቱ ሳይደበዝዝ እዚህ የደረሰ የብሔረሰቡ የማንነት መገለጫም ነው፡፡
ህንግጫ በኮንታ ብሔረሰብ አጠራር ያማረ፣ ያጌጠ፣ የለመለመ ማለት ሲሆን አደይ አበቦች ፈክተው የሚታዩበት፣ የክረምቱ ወራት አልፎ የጠራ ሰማይ የሚታይበት፣ አርሶ አደሮች የክረምት አዝመራቸውን አገባደው ከአረምና ኩትኳቶ ስራ አርፈው ለመልካም ፍሬ ተስፋ የሚሰንቁበት ወቅት በመሆኑ በብሄረሰቡ ዘንድ በልዩ ትኩረትና በተስፋ የሚከበር ልዩ በዓል ነው።የህንግጫ በዓል ሲከበር ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ እንደመሆኑ በዕለቱ ሁሉም ጠግበው፣ ጎዶሎው ሞልቶ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ የሚበላበት፣ ድሃ ከሀብታም እኩል የሚያከብሩት፣ መጥፎ ነገር ሁሉ ቀርቶ መልካም መልካሙ እንዲሸጋገር ፈጣሪውን የሚለምንበት የጥጋብና ሙሉ የመሆን አስተምህሮ የሚገለፅበት የተስፋ በዓል ነው።
እንደ ባህሉ ትውፊት ህንግጫ ከጳጉሜ የመጨረሻዋ ቀን እስከ መስከረም 30 ድረስ ደምቆ ይከበራል። ከቤት እስከ ደጃፍ አካባቢ ይፀዳል፤ ከአሮጌው ዓመት የሚሻገር እድፍና ጉድፍ እንዳይኖር ይጠረጋል፤ ምድር ትዋባለች፡፡ህንግጫ ከ12 ዓይነት በላይ የሆነው የኮንታ ባህላዊ ምግብ ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት የባህል አውድም ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ እሳት የሚወጣው ጳጉሜ የመጨረሻዋ ቀን ነው፡፡
በህንግጫ ወቅት ‹‹ሙጬ ›› ማለት ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 5/6 ድረስ ያሉ ቀናትን የሚያመላክት ሲሆን በእነዚህ ቀናት ዉስጥ እህል በተለይም ጤፍ ቢዘራ የማይበቅልና ቢበቅልም እንኳን ከግንዱ ተቆርጦ የሚወድቅና እንዲሁም ሳያድግ ቀጭጮ ስለሚቀር ወቅቱ ‹‹ ሙጬ ›› ተብሏል፡፡ በመሆኑም ‹‹ ሕንግጫ ›› የሚለዉ የብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል እንደሆነ የዕድሜ ባለፀጋዎችና የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍቶች ይመሰክራሉ፡፡
የኮንታ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ማክበር የጀመረዉ በኦሞ፣ በጎጀብ እና በዝግና ተፋሰስ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዓሉን ሲያከብሩ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ሆኖም በዓሉ መቼና እንዴት ተጀምሮ እያደገ እንደመጣ ትክክለኛውን ጊዜ የሚጠቁም የጽሑፍ መረጃ ባይኖርም ለበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ የራሱ አመልካች መረጃዎች እንዳሉ ቀደምት አባቶች በአፈ-ታሪክ ያረጋግጣሉ፡፡ይህም በኮንታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም የመጀመሪያው የአራ የዘር ግንድ ቀዳሚ ንጉስ “ከካቲ ኤማዶ” ዘመነ መንግስት በ12ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ ከጎረቤት ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን እያከበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆኑ በታሪክ ይነገራል፡፡
‹‹ህንግጫ›› ማለት እንደ ብሔሩ አባቶችና የታሪክ ምሁራን አገላለጽ የሁለት ቃላት የ‹‹ሂን›› እና የ‹‹ጊጫ›› ዉህድ ሲሆን ‹‹ሂን›› ማለት ወደዚያ አስፋ/ፊ ሲሆን ‹‹ጊጫ›› ማለት አሳምር፣ ጥረግ፣ አጽዳ፣ ፋቅ (Giid’ara) የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በመሆኑም ከዕለቱ በዓል ጋር የሚያያዝበት ምክንያት ጎረቤት በዓሉን አብሮ ለመታደም፤ ወጣቶች በበዓሉ ወቅት ለጭፈራ እና ለምርቃት ሲመጡ ባማረና ጽዱ በሆነ አካባቢ እንዲያከብሩ እንዲሁም በዓሉ ሲከበር እንግዳ ለመቀበል ለመመራረቅ ከየጎረቤቱ አዲስ ዓመትን ለማክበር እና አዲሱን ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከርሃብ ወደ ጥጋብ ሲሸጋገሩ ብሩህ ተስፋን ሰንቀዉ በእርቅና በጥጋብ ለምድሪቱ ሠላምን፣ በረከትን፣ ፍቅርን፣ ጤንነትን፣ በመመኘት የሚቦርቁበት አካባቢ መሆኑን ያሳያል፡፡
አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ አመልካች በመሆኑ ያንን ለማመልከት የተጠቀሙት ቃል ሲሆን ከበዓሉ ዝግጅት ጋር ይያያዛል፤ ይኸዉም ደጃፍ (Zabba) kariya Aassade Giic’c’aa፣ ለበዓሉ ከሚዘጋጅ የምግብ ዓይነቶች ዉስጥ አንዱ አንጮቴ ወይም Ushshushiya Giic’c’aa እና በበዓሉ ተዉቦና ደምቆ ለመታየት እንሶስላ ወይም wusoluwa Giic’aa ከሚለዉ ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡የኮንታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለዉ ሲሆን የዘመን አቆጣጠር የመጀመሪያ የመስቀል ወር / Mask’ala Aginaa / ይባላል፡፡
በህንግጫ በዓል አከባበር ወቅት ወጣቶች ከሚጫወቱት ጨዋታዎች ለአብነት “Hoyabee salo, wod’aassaa wosikkee , andoli bole, wohee baabo baabo, koole kooli godaa” ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የህንግጫ በዓል እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ጎረቤት የተጣላ ሳይታረቅ ቂም በመያዝ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ስለሌለበት የተጣሉ ግለሰቦች በጎረቤት ሽማግሌ በተለይም በ’ሙጬ’ /በጳጉሜ/ ቀናት ይቅር ለእግዚአብሔር ይባባላሉ፡፡ ከቤት ርቆ ያለም ሆነ ከቤት ዉጭ ያለ ማንኛዉም የቤተሰብ አባል ወደቤት ሳይገባ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” ስለማይወጣና ዉጭ ከቀረ በዚያዉ ይቀራል ተብሎ ስለሚታሰብ የግድ ወደቤት ከገባ በኋላ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” በመያዝ እርኩስ መንፈስ ዉጣ እያለ ከዚህ በታች በተገለጸዉ መልክ ይፈፀማል፡፡
የትርኳሹን እጄታ በእጅ በመያዝ እና በማወዛወዝ ወደ ዉጭ የሚያወጣዉ አባወራ ለአዲሱ ዓመት ያደረሰዉን ፈጣሪ እያመሰገነና መጪዉ ዘመን የደስታ፣ የፍቅር፣ የጤንነት፣ የሠላም፣ የአንድነትና የጥጋብ እንዲሆን እየተማፀነ እቤት ዉስጥ ያለዉ የአሮጌዉ ዘመን ክፉ መንፈስ እንዲወጣ እያንዳንዱን የቤት ዉስጥ ቁሣቁስ መኝታዉን፣ መከታዉን፣ ምሰሶዉን፣ ወጋግራዉን፣ የከብቶችን በረት (ከበሬ ጫንቃ፣ ከላሞች ግት)፣ መዉጫ በሩን በትርኳሹ እየነካካ ‹‹የረሃብ የበሽታ የጥላቻ ክፉ መንፈስ ከዚህ ቤት ዉጣ›› እያለ ካዳረሰ በኋላ ትርኳሹን ከቤት አዉጥቶ ወደ ዉጭ አርቆ ይወረዉራል፡፡ትርኳሹ (Ts’iifaa) በሚወጣበት ቀን በዕለቱ ለእራት የሚዘጋጅ ምግብ ማብሰያዉን ሞልቶ ይዘጋጃል፤ እንዲሁም በቤት ዉስጥ ያሉ የምግብም ሆነ የዉሃና የወተት ዕቃዎች ተሟልተዉ እና ተከድነዉ ማደር አለባቸዉ፤ ምክንያቱም እነኝህ ቁሳቁሶች ጎደሎ ሆነዉ የሚያድሩ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ ችጋርና ርሃብ ከቤት አይወጣም ተብሎ ይታመናል፡፡
የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ በአካባቢዉ ታዋቂ ወይም የዕድሜ ባለፀጋ በሆኑ አባቶች ቤት በመጀመሪያዉ ቀን በጋራ ይከበራል፤ በበዓሉ አከባበር ቀን የሚወጣዉ ትርኳሽ በችቦ መልክ ሣይሆን በምድጃ ዉስጥ አየነደደ ካለዉ የማገዶ ጉማጅ ከነፍሙ ተመዞ በመያዝ ይወጣል፡፡የዚህ ጉማጅ ስም በአካባቢዉ አጠራር “ፂፋ” ይባላል፡፡ ከዚያም በኋላ የቤተሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ ጎረቤቶች እንደየ ዕድሜያቸዉ ቦታ ቦታቸዉን ከያዙ በኋላ የእድሜ ባለፀጋ የሆኑ ከ1-3 በሚደርሱ ሽማግሌዎች ምርቃት ይደረጋል፡፡ምርቃቱም፡- የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ቀርበው “ቦርዴ” በትልቅ እንስራ አሙልቶ በማፍሰስ በሴቶች እልልታ ታጅቦ ጠላዉን ለእያንዳንዱ ታዳሚ በማዳረስ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡
ሞልቶ ከተቀመጠው እንስራ በዋንጫ የተቀዳ ጠላ በመጀመሪያ የተሰጣቸዉ የዕድሜ ባለፀጋዎች ይመርቃሉ። በአሮጌዉ ዓመት ሲያጣላ፣ ሲያጋጨን የነበረዉ ክፉ መንፈስ ከመኃላችን ፈጣሪ ያርቅልን! ይህ ጠላ ሞልቶ እንደፈሰሰ ሁሉ ጤንነት፣ ፍቅር፣ ሠላምና ጥጋብ በሀገራችን በአካባቢያችን በሰፈራችን እንዲሁም በእያንዳንዳችን ቤት እንዲዚህ ሞልቶ ይፍሰስ!አዲሱ ዓመት የሕዝቡ እና የመንግስት አንደበት የሚጣጣምበት፣ ዘርተን የምንቅምበት፤ ወልደን የምንስምበት፤ ነግደን የምናተርፍበት፤ ከቤት የወጣዉ በሰላም የሚመለስበት፤ ያፈራነዉን በሰላም በፍቅር የምንበላበት ዘመን ያደርግልን! በአዲሱ ዓመት ስትወጡ እንቅፋት አይምታችሁ፤ ስትናገሩ እዉነተኛ ሃሳብ አይጥፋባችሁ፤ ፍቅራችን እንደ ሰማይ ጉም እንደ ምድር ሰርዶ እንደ ጉንዳን ሕብረትና አንድነት እግዚአብሔር ያድለን! በመጨረሻም ከእኛ የተረፈዉን እግዚአብሔር ይመርቃችሁ በማለት ያጠቃልላሉ።
በዚህ ዓመትም በጳጉሜ 1 የህንግጫ በዓልን በአደባባይ ለማክበር አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡

የት/ቤቶችን ደረጃ ማሳደግና በትምህርት ዘርፍ እየታየ ያለውን ውጤት ለማጠናከር በበለጠ ቁርጠኝነት ማስፈፀም ከሁሉም ይጠበቃል፤ አቶ ታከለ ተስፉየኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2019 ትምህርት ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በዞኑ በ2019 ትምህርት ዘመን ከ47 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ ለማስተማር ታቅዷል።መድረኩን የመሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ የትምህርት ስራ ትውልድ ላይ የሚሰራ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግ በማንሳት ይህንን በመገንዘብ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።የትምህርት ስራ አድካሚና ብዙ ልፋት የሚፈልግ ብሎም በትውልድ ላይ በሚታየው ውጤት የሚለካ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ታከለ በቀጣይም አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች የጎላ ሚናቸውን በመወጣት ትምህርት ቤቶች በግብዓት የተሟሉና ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የሚጠበቀው ውጤት እንዲመጣ መትጋት እንደሚያሻ አስገንዝበዋል።
ይህንንም በበለጠ ቁርጠኝነት ማስፈፀም ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ጥራት መሠረት የሚጥሉ ቁልፍና አበይት ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በተለይም የስርዓተ ትምህርት ለውጥና የት/ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስራዎች በትኩረት መሰራታቸውን ተናግረው እንደዞንም ቅድመ 1ኛ ት/ቤትና አዳሪ ልዩ ት/ቤት ግንባታ፣ የመጽሐፍት ህትመት እና መሠል ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።በዞኑ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ በደረጃ 1 እና 2 ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የት/ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ያሉት አቶ አጥናፉ በ2019 ትምህርት ዘመን የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማስቀጠል፣ የማህበረሰብና የልማት ተቋማት ተሳትፎ ማሳደግ፣ የትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢ ማጠናከር፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን ማሻሻልና መሠል ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።
በ2019 በጀት ዓመት 10 ሞዴል ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች እንደሚገነቡ በመጠቆም ከዝግጅት ስራዎች ጎን ለጎን የክረምት ድጋፍ ትምህርት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።ለተግባራቱ ውጤታማነትና ሀገር ተረካቢ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ እንዲፈጥሩ መላው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።የመድረኩ ተሳታፊዎች በዞኑ የትምህርት ስራ ተጨባጭ ውጤት እየታየበት እንደሚገኝ ተናግረው ከዚህም በላይ በስነ ምግባር የታነፀ፣ ስራ ወዳድና ስራ ፈጣሪ ትውልድ እንዲቀረፅ በበለጠ አቅም መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በዞኑ በትምህርት ዘርፍ ድጋፍና ክትትል ማጠናከር፣ የሀብት አጠቃቀም ማሻሻል፣ የመ/ራን አቅም ማጎልበትና መሠል ስራዎች የበለጠ ትኩረት እንደሚሻቸው አመላክተዋል።በመድረኩ የ2019 ትምህርት ስራ በተያዘለት ዕቅድ እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጧል።ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።
ወቅታዊ፣ሀገራዊና ዞናዊ የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት የፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ

