
- የጨበራ ጩርጩራ ብ/ፓርክ በክልላችን ከሚገኙት ዋና ዋና ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ ሲሆን ካለው ዕምቅ ከተፈጥሮ ሀብት አንፃር በቀዳሚነት ስሙ ይነሳል፡፡
- 1410 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የቆዳ ስፋት ሲኖረው አብዘኛው የፓርኩ አካልና መስህብ በኮንታ ዞን ይገኛል፡፡ ከዞኑ ዋና ከተማ አመያ በ13 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ቱሪስቶች ብዙም ሳይጉላሉና ሳይለፉ በቀላሉ ጎብኝተው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባለፈ ፓርኩን በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደርና የዱር እንስሳትን በቅርበት ለመከታተልና ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
- የጨ/ጩ/ብ/ፓርክ በብሔራዊ ፓርክ ደረጃ የተቋቋመው በ1997 ዓ/ም በአካባቢ ህብረተሰብና በአስተዳደር አካላት ጥያቄ መሠረት ካለው ከቱሪዝም ሀብት አንፃር የተመዘገበ ሲሆን በይፋ ሥራ የጀመረው ከ2 ዓመት በኋላ በ1999 ዓ/ም ነው፡፡
- የፓርኩ ርቀት ከአ.አ በጅማ በኩል 442 ኪ.ሜ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 80 ኪ.ሜ ብቻ ፕስታ ስነጠፍ ቀሪው በሙሉ የአስፓልት መንገድ ተጉዘው አስደናቂውን የፓርኩን ተፈጥሮ ያገኛሉ፡፡ ከጊዜያዊ የክልሉ ዋና ከተማ ከቦንጋ በጅማ በኩል 215 ኪ.ሜ ሲጓዙ ፓርኩ ጋር ይደርሳሉ፡፡
የዱር እንስሳትን በተመለከተ እስካሁን በተደረጉ ውስን ጥናቶች በብ/ፓርኩ
- 40 ትልልቅና መካከለኛ አጥቢ የዱር እንስሳትና ከአውራሪስ በቀር በዘርፉ ግዙፍ አምስት ከሚባሉ አራቱ ትልልቅ እንስሳቶች ማለትም የአፍሪካ ዝሆን፣ ጎሽ፣ ነብርና አንበሳን በጥሩ ሁኔታና ቁጥር ይገኙበታል፡፡
ሌሎች አጥቢ የዱር እንሳሳት ለአብነትም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ተኩላ (wild dog)፣
- ትልቁ የዱር አሳማ፣
- አቦሸማኔ፣
- ጉማሬ፣ አዞ የሚገኙ ስሆን
- 18 ትናንሽ አጥቢ የዱር እንስሳት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡
በብ/ፓርኩ 138 የአዕዋፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስቱ አገራችን ከኤርትራ ጋር ብቻ የምትጋራቸው የአዕዋፍ ዝርያዎች ናቸው፡፡

- ብ/ፓርኩ ሰፊ ጥናት ቢደረግበት በርካታ የዱር ህይወት ዝርያዎች ሊገኙ የሚችል ሲሆን ለአብነትም በ2010 እ.ኤ.አ. በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝና
- ጋራ ጨበራ የተሰኘ አንድ ወርቃማ የዓሳ ዝርያ
- እንዲሁም
- Harvey’s duiker and weyns duiker የሚባሉ ሁለት የሚዳቋ ዝርያዎች በአገራችን ኢትዮጵያ በጨበራ ጩርጩራ ብቻ የሚገኙ ብርቅዩ ሆኖ ተመዝግቧል ፡፡
- የእጽዋት ሽፋን
- የእጽዋት ሽፋኑ በአራት ምድቦች የተከፈለ ሲሆን እነዚህም
- እንጨት ለበስ የሳር መሬት (62%)፣
- የተራራ ላይ ደን (29%)፣
- የወንዝ ዳር ደን (3%) እና
- እንጨታማ መሬት (5%) ናቸው፡፡
- እስካሁን በተደረገው አንድ ጥናት 106 እንጨታማ የእጽዋት ዝርያዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

- ሀጌ የማዕድን ውሃ በጨበራ ጩርጩራ ብ/ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህቦች አንዱ ነው፡፡ የሀጌ ማዕድን ውሃ ከፓርኩ ጽ/ቤት በ8 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የሀጌ ማዕድን ውሃን ተደናቂ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉት፡፡ ለአብነት ያህልም ውሃው ከመሬት የሚወጣበት ቀዳዳዎች በቁጥር ከ4-5 የሚደርሱ ሲሆን እነዚህ ሁሉ አንድ የእንስራ አፍ በምታክል ጠባብ ጉርጓድ መውጣታቸውን ላየው ሰው ልዩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡
- የሀጌ ማዕድን ውሃ ከመሬት ውስጥ ሲወጣ ምንም የለለበት ንፁህ ውሃ ሲሆን ከተወሰኑ ሰዓታት በኃላ ወደ ብረት ዝገት ተቀይሮ ዙሪያ ላይ ሲቀመጥ ያገኙታል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ከፍተኛ የማዕድን ክምችት በመሬት ውስጥ ከመኖሩ የተነሳ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
- የሀጌ ማዕድን ውሃን ከፍል ውሃ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ብኖር ሁለቱም እየተፍለቀለቁ ከመሬት ውስጥ የሚወጡ ሲሆን ልዩነታቸው ደግሞ ሀጌ የማዕድን ውሃ ቀዝቃዛ ሲሆን ፍል ውሃ ግን በተቃራኒው በጣም ይሞቃል፡፡ በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች አብዛኛውን ጊዜ ከንፁህ ውሃ ይልቅ ይህን የማዕድን ውሃ ለመጠጣት ይመርጣሉ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ምንም ዓይነት ጀርድያም ሆነ ሌሎች የውሃ ትላትሎች ስለማይኖሩ ነው ብሎ ይናገራሉ፡፡

- የከሪ በላ ሐይቅ በኮንታ ዞን ከሪ በላ ባደጉቻ ቀበሌ ይገኛል፡፡ የከሪ በላ ሐይቅ በዞን ውስጥ ከሚገኙ አምስት (5) የተፈጥሮ ሐይቆች አንዱ ሲሆን ከዞን ዋና ከተማ /አመያ/ በ28 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
- ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የተንጣለለው የከሪ በላ ሐይቅን ከሌሎች ሐይቆች የሚለየው ነገር ብኖር ዙሪያውን እንደ አጥር ያካለለው አረንጎዴ የደን ሽፋንና በዋናነት ዕድሜ ጠገብ ዘንባባዎች ለየት ያለ ውበት አጎናጽፎታል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጉማሬ ዝሪያ በዚህ ሐይቅ ውስጥ መኖሩም የሐይቁን ተደናቂነት ያጎለዋል፡፡

- የሾከላ ዋሻ ፏፏቴበዞኑው ውስጥ ካሉት ዋሻዎች በስፋት ከፍተኛ ቦታ ይይዛል፡፡ ሾከላ የሚለውን ስያሜ ያገኘውም ከዋሻው አናት ላይ በግምት ከ40-50 ሜትር በላይ ርቀት ወደታች የሚወረወረው ሾኬላ በተባለው ፏፏቴ ስም እንደተሰየመ ይነገራል፡፡ ዋሻው ሁለት ሲሆን ከአንዱ ዋሻ ወደ ሌላው ዋሻ ለመድረስ 100 ሜትር ያስከዳል፡፡
- የመጀመሪያው ዋሻ ሦስት ትላልቅና ስድስት ትናንሽ ክፍሎች አሉት፡፡ የዋሻው ስፋት በግምት 80×60 ሜትር ሲሆን የመግቢያ በሩ ከፍታ ሦስት ሜትር ያህል ነው፡፡ የዋሻው ሁለተኛ ክፍል የመኖሪያ ቤት 2 ሣሎን እንደሚባለው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ክፍሉ በግምት 15×20 ሜትር የሚሆን ስፋት አለው፡፡ ይህ ክፍል ከሦስተኛ ክፍል ጋር ተጠርቦ የተሰራ በሚመስል ድንጋይ የተከለለ ነው፡፡
- የዋሻው ሦስተኛው ክፍል ሰፋ ያለ ሲሆን በውስጡ የተለያዬ ቅርጽ ያላቸው ተክል ድንጋይ የሚመስሉ ከዋሻው ጣሪያ በሚንጠባጠበው የውሃ ጠብታ ከሚመስል ፈሳሽ የተሰሩ ውበት ያላቸው ጌጣጌጦች ያሉት ክፍል ነው፡፡ በግራ በኩል ስድስት ትናንሽ ክፍሎች ሲኖሩት ባለሙያ ተጨንቆና ተጠቦ የተሰራ የህንፃ ስሪት ይመስላሉ፡፡ በዋሻው ቀኝ በኩል እየተመመ የሚወርደው የሾኬላ ፏፏቴ ለዋሻው ለየት ያለ ውበት ሰጥቶታል፡፡ ዋሻው የተፈጠረበት ትክክለኛ ዘመን ባይታወቅም ብዙ ዘመን እንዳስቆጠረ አይቶ መገመት ይቻላል፡፡

- ቡልአ ፏፏቴ በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ ስሆን ከወረዳዉ ዋና ከተማ ኮይሻ በ25 ኪ.ሜ ርቀት በስተ ምስራቅ አቅጣጫ ልዩ ስም ቡልአ ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ ይገኛል፡፡
- ፏፏቴዉ እየተምዘገዘገ በተፈጥሮ ጥርብ ድንጋይ አለት ላይ እያረፈ የሚወርደዉ ከ250 ሜትር በላይ እርዝመት ያለዉ ሲሆን ፏፏቴዉን አስገራሚና አስደሳች ከሚያደርጉት ክስተት አንዱ ነዉ፤ በመሆኑም ፏፏቴዉ ከወረዳዉ ወጣ ብሎ ስለሚገኝ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ከተቻለና በፏፏቴዉ ዙሪያ የመዝነኛ ማዕከል ቢቋቋም ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ገቢ ማስገኘቱ የማያጠራጥር ነዉ፡፡
- የፏፏቴዉ መነሻ ከቡልአ ወንዝ ልዩ ስም ማስቶቃ ከሚባልበት መንደር ሲሆን ከ250 ሜትር በሚደርሰዉ ከፍታ ከቁልቅለታማ የተፈጥሮ ጥርብ የድንጋይ አለት እየተፈናጠረ ስወርድ የነጎድጓድ ድምጽና አከባቢዉን እንደ ጢስ የሚሸፍን የዉሃ ብናኝ ይስተዋላል፡፡
- በተጨማሪ ይህንን ፏፏቴ ልዩ የሚያደርገዉ ወደ ታች የዉረደዉ ዉሃ ኮይሻ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግንባታ በመግባት የሃይል አቅርቦት ለማሳደግ የድርሻዉን እየተወጣ የሚገኝ ፏፏቴ ነዉ፡፡

የተፈጥሮ ድንቅ የሆነውን #የባርቦ_ፏፏቴን በጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ ይጎብኙ! ተፈጥሮ በልግስና የሰጠችውን ውበት ለመቋደስ ዝግጁ ነዎት? ከከተማው ግርግር ወጣ ብለው፣ ንጹህ አየር በመተንፈስ፣ ልብን በሚያረካ የተፈጥሮ ድምፅ መታደስ የሚፈልጉ ከሆነ መድረሻዎ የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ ነው።
#ምን_ይጠብቀዎታል?
የዱር እንስሳት ዝሆን፣ አንበሳ፣ ጎሽ፣ ጉማሬ፣ አቦሸማኔ … እና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎች እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የባርቦ_ፏፏቴ_ልዩ_ገጽታ፡ ከከፍታ ቦታ እየተምዘገዘገ የሚወርደው የባርቦ ፏፏቴ፣ ለአይን በሚፈጥረው ማራኪ እይታ እጅግ አስደናቂ ነው። የፏፏቴው ውበት ለመንፈስዎ እረፍት፣ ለዓይንዎ ደግሞ የማይረሳ ትዝታን ይሰጣል።ተንጠልጣይ_ድልድይ፡ ፏፏቴውን ከላይ ሆኖ ለመታዘብና አስደናቂውን የተፈጥሮ ድንቅ በአእዋፋት እይታ (Bird’s eye view) ለመቃኘት፣ በቦታው የተዘጋጀውን ተንጠልጣይ ድልድይ ይሻገሩ። ልብ የሚሰቅል፣ ነገር ግን እጅግ አስደሳች የሆነ ተሞክሮ ይጠብቀዎታል።
የተፈጥሮ_ጥበብ፡ ፏፏቴው በታላቅ የጥበብ እጅ እንደተቀረጸ በሚያስቆጥር የድንጋይ አምባ የታጠረ ነው። እንደ ዘብ የቆሙለት እድሜ ጠገብና እርስበርስ የተጋመዱ ግዙፍ ዛፎች ደግሞ ለቦታው ድንግልና እና ውበት አዲስ ድምቀት ሰጥተውታል። ለምን_ይጎብኙን?
ይህ ስፍራ ከዕለት ተዕለት ውጥረት ለመላቀቅ፣ በተፈጥሮ እቅፍ ውስጥ በመሆን አዲስ ጉልበት ለመሰብሰብ እና የኢትዮጵያን ድብቅ ውበቶች ለመታዘብ ተወዳዳሪ የለውም።

በኢትዮጽያ ከሚገኙ ቀደምት ቤተክርስቲያናት አንዷ እንደሆነች ከትውፊት የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከኮንታ ዞን ዋና ከተማ በአማካይ 16 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ሲገኝ ከቦንጋ በ215 ኪ/ሜ እና ከአ.አ ደግሞ 486 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያኑ አመሰራረትም በወቅቱ በአንጃ መሪ በነበረው በራስ ወ/ጊዮርጊስ አማካይነት በ1882 ዓ/ም የተቋቋመ እና የቤተክርስቲያኑ ጽላት የመጣው በአባ ተክል ወ/ጽድቅ እና መምህር ስመር ወ/ጽድቅ በሚባሉ ሊቃነ ካህናት ከሰሜኑ ክፍል እንዳመጡት ይነገራል፡፡ ይህ ቅዱስ ስፍራ ከዞኑው ከተለያዩ አቅጣጫ የሚመጡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ምዕመናን በየአመቱ ህዳር 12 እና ሰኔ 12 ቀን ፅላቱን በማውጣት ስርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት እንዲሁም አዘወትረው ሕዝብ ፀሎት የሚያደርሱበትና ከተለያዩ በሽታዎች የእምነት ፈውስ የሚያገኙበት ቦታ ነው፡፡
- በዚህ ቤተክርሲቲያን አሰገራሚ ከነበሩ ጉዳዩች አንዱ 134 ዓመት ያስቆጠረውና ዛሬም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የጣሊያን የበር ቁልፍ አንዱ ነው፡፡
- ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከተራራው ዝቅ ብሎ ኮረብታማ ቦታ ላይ የተሰራ ሲሆን የተለያዩ ስፋት መጠን ያላቸው ሦስት ክፍሎች (ቅኔ ማህሌት ፣ መቅደስና ቅድስት) ስምንት አምዶች፣ ሶስት በሮችና ሁለት መስኮቶች አሉት፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን ዕድሜ ጠገብ በሆኑ ሀገር በቀል ትላልቅ ጥዶች ፣ባህር ዛፎች፣ዋንዛዎች ወዘተ—-ዛፎች እንዲሁም በስተ ደቡብ ምዕራብ ሰማይ ጠቀስ ተራራ ላይ በበቀሉ የበረሃ ዛፎች ተሸፍኖ ይገኛል፡፡
- በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ በብራና ተለብጠው በዚያን ጊዜ የነበረውን የፊደል አቀማመጥ እንደያዙ በቁም የተሰሩ ፊደላት በግዕዝና በአማርኛ ሲሆን ሌሎችም ንዋየ ቅዱሳን መጽሐፍት ይገኛሉ፡፡ እስከ ዛሬ ውበታቸውን ጠብቀው ይገኛሉ፡፡ የጥንት ዝክረ ታሪክ የብራና ላይ ቅርሶች የሚያውሱት ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል መዝሙረ ዳዊት፣ መጽሐፈ ግንዘት፣ መልክአማሪያም (መልክአ ኢየሱስ)፣ መጽሐፈ ዝቅ፣መጽሐፈ ክርስትና፣መጽሐፈ ሰዓታት፣ መጽሐፈ መልክአ ኦዶም ፣ መልክአ ውዳሴ፣ መጽሐፈ አልጋኖ፣መጽሐፈ ክዳን፣ ቅዱስ ወንጌል መጽሐፈ፣መጽሐፈ ቅዱስ ወዘተ—በታሪክ የተመዘገቡ ጥንታዊ የግዕዝ እና አማርኛ የብራና ቅርሶች በቤተክርስቲያኑ የሚገኙ ሲሆን ሌሎችም ንዋየ ቅዱሳን መጽሐፍት ይገኛሉ፡፡
- ሌላው ደግሞ የዚህች ቤተክርስቲያን ገፀ በረከቶች የአሁኑ ታሪካዊ የእምነት መከወኛ ቅርሶች ፅናፅሎች፣የነሀስና የብር ምስሎች፣ የእንጨት፣ የነሀስና የብር ፅዋዎች የነሀስ ቃጪል፣ከበሮ ወዘተ—የተለያዩ እድሜ ጠገብ ጥንታዊ ቅርሶች ተሰብስበው መገኘታቸው ታሪካዊ ቅርሶችን መንከባክብ፣መጠበቅና ማልማት ብሎም ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ ይመለከተኛል ለሚል ሰው ሁሉ አደራው የበዛ ነው እንላለን፡፡
ስለዚህ ይህንንና መሰሎቹን ውብና ድንቅ ቅርሶቻችንን በዞኑው ብቻ ሳይሆን የሀገር ሀብት እንደመሆኑ መጠን በመንከባከብ፣ በመጠበቅ፣ በመመዝገብ፣ በመሰነድ በማልማትና በማስተዋወቅ ወደ ቱሪዝም ገበያ ከማስገባትም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመስራት የሁላችን የጋራ ጥረት ከታከለበት ከምንም በላይ የሰው ደራሹ ሰው ነው እንደሚባለው ለቅርሶችም ሰው መሆኑ ማረጋገጥ እንችላለን ማለት ነው::

በኮንታ ዞን ታሪካዊ እና ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በአንጋፋነታቸዉ ከሚታወቁበት ቅዱስ ስፍራዎች ዉስጥ የገንጅ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አንዱ ነዉ፡፡ ከዞኑ ዋና ከተማ አመያ በአማካይ በ14 ኪ/ሜ ርቀት ላይ እና ወደ ጭዳ በሚወስደዉ የመኪና መንገድ በስተቀኝ በኩል 2 መቶ ሜትር ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያኑ አመሰራረትም በወቅቱ በአንጃ መሪ በነበረው በራስ ወ/ጊዮርጊስ አማካይነት ከሰሜን ሸዋ ሸንኮራ የመጣው ይህ ጽላት ከሰሩ ሆነው ሲያሰተዳደር በነበረው በደጀ አዝማች አሰፋ አማካይነት በ1883 ዓ/ም የተቋቋመ እንደሆነ አፈታሪክ ተነጋሪዎች ይነገራሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ኮረብታማ ቦታ ላይ የተሰራ ሲሆን የተለያየ ስፋት መጠን ያላቸው ሦስት ክፍሎች (ቅኔ ማህሌት ፣ መቅደስና ቅድስት) ሃያ አምዶች፣አራት በሮችና ስምንት መስኮቶች አሉት፡፡ ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ዕድሜ ጠገብ በሆኑ ሀገር በቀል ትላልቅ ሽበታማ ጥቁር እንጭት፣ጥዶች ፣ባህር ዛፎች፣ዋንዛዎች፣ዝግባዎች፣ብሳነዎች ወዘተ—-ዛፎች እንዲሁም በስተ ምስራቅ በኩል በጠብቅ የበረሃ ዛፎች ተሸፍኖ ይገኛል፡ በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ በብራና ተለብጠው በዚያን ጊዜ የነበረውን የፊደል አቀማመጥ እንደያዙ በቁም የተሰሩ ፊደላት በግዕዝና በአማርኛ ሲሆን ሌሎችም ንዋየ ቅዱሳን መጽሐፍት ይገኛሉ፡፡ እስከ ዛሬ ዉበታቸዉን ጠብቀዉ ይገኛሉ፡፡ የጥንት ዝክረ ታሪክ የብራና ላይ ቅርሶች የሚያውሱት ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል መጽሐፈ ግንዘት፣መጽሐፈ ቅዳሴ፣መጽሐፈ ጊዮርጊስ፣ ወዘተ—ሲሆን እንዲሁም የእምነቱ መከወኛ ቅርሶች ጥንታዊ አልባሳት፣ከነሐስ የተሰሩ መስቀሎች ይገኛሉ፡፡ስለዚህ ይህንንና መሰሎቹን ውብና ድንቅ ቅርሶቻችንን በዞኑ ብቻ ሳይሆን የሀገር ሀብት እንደመሆኑ መጠን በመንከባከብ፣ በመጠበቅ፣ በመመዝገብ፣ በመሰነድ በማልማትና::
በማስተዋወቅ ወደ ቱሪዝም ገበያ ከማስገባትም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመስራት የሁላችን የጋራ ጥረት ከታከለበት ከምንም በላይ የሰው ደራሹ ሰው ነው እንደሚባለው ለቅርሶችም ሰው መሆኑ ማረጋገጥ እንችላለን ማለት ነው::
Chebera Elephant Paw Lodge – A naturally endowed treasure trove!

