ኢንቨስትመንት
የኢንቨስትመንት ዘርፍን ማጠናከር ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ተመራጭ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷ ይህንኑን ያሳያል፡፡ በዚህም መሰረት ከአጠቃላይ ከሀገሪቱ ውስጥ ገቢ ከግማሽ በላይ ከአግሮፕሮሰሲንግ ሴክተር የሚመነጭ መሆኑ እንዲሁም ከ80% በላይ የኤክስፖርት ገቢና 85% የስራ እድል በዚህ የሚሸፈን መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዉጥኖችን ከዳር ለማድረስና የህዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የሚችሉ ባለሀብቶች በመንግስት ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተመርተዉ መዋዕለ ነዋያቸዉን ሲያፈሱ በመሆኑ መንግስት ይህንን ዘርፍ ያበረታታል፡፡ ቁጥሩ ዕለት ተዕለት የሚያሻቅበዉ ስራ አጥ እጁን ከስራ ጋር አገናኝቶ ሰርቶ ራሱን እንዲለዉጥ በማድረግ ረገድ ከመንግስት ባልተናነሰ የባለሀብቶች ሚና የጎላ ነዉ፡፡
በሰለጠነዉ ዓለም አብዛኛዉ ሰራተኛ ሰርቶ የተሻለ ክፍያ የሚያገኘዉ በግል ባለሀብቶችና ኩባኒያዎች ተቀጥሮ ሲያገለግል ነዉ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 6 ዞኖች አንዷ የሆነችዉ ኮንታ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓት በርካታ ሀብቶችን በዉስጧ የያዘች ሲሆን ለኢንቨስትመንት የተለየዉ አጠቃላይ የመሬት ሽፋን 10,139 ሄክታር ነዉ:: ከዚህ ውስጥ 20 ለሚሆኑ እንቨስተሮች ከ6,558.7 ሄ/ር መሬት በላይ ተላልፎላቸው በማልማት ላይ የሚገኙ ሲሆን ለአካባቢዉ ህ/ሰብ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የተክኖሎጂ ሽግግር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ዉድ የዎይታ መጽሔት አንባቢዎቻችን በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተዉ ከሚገኙት ባለሀብቶች ዉስጥ ለአብነት በኮንታ ኮይሻ ወረዳ ኦሽካ ዴንቻ ቀበሌ ላስቴ ተራራ ስር በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብት አቶ ግርማ እሸቴ በ2011 ዓ.ም በዞኑ ኦሽካ ዴንቻ ቀበሌ ለኢንቨስትመንት አገልግሎት ከወሰዱት 400 ሄ/ር መሬት በ150 ሄ/ር ላይ ቡና እና ፍራፍሬ በተሻለ ደረጃ እያመረቱ ሲሆን ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የስራ ዕድል በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘዉን ጥቅም ለማግኘት በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም አለማየሁ ከተማ በጠቅላላ እርሻ ዘርፍ በቶልካ ቀበሌ 2000 ሄ/ር መሬት ወስደዉ አሁን ላይ 300 ሄ/ር መሬት ላይ ሰብል በማልማት የተሻለ ዉጤት እያስመዘገቡ ይገኛል፡፡ ዞኑ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በማዕድን ልማትና በሌሎችም ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸዉን ለማፍሰስና ከዘርፉ ዉጤታማ መሆን ለሚሹና መስፈርቱን አሟልተው ለሚመጡ ባለ ሀብቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሩን ክፍት አድርጎ እየተጠባበቀ ይገኛል፡

